top of page

ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር

Updated: Jan 6, 2023

1ኛ ትምህርት የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል -

ክርስቲያን እንደመሆናችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት አስደናቂው ነገር በምድር ላይ የእርሱን ሥራ እንድናስተዳድር በእኛ ላይ እምነት መጣሉ ነው። ከሰብአዊ ዘር ታሪክ ጅማሬ ጀምሮ እግዚአብሔር እንከን የሌለውን ፍጥረት እንዲንከባከቡ (እንዲጠብቁ) ለአዳምና ሄዋን ሀላፊነት ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 2፡7-9፣ 15ን ይመልከቱ)። ለእንስሳቶቹ ስም ከመስጠት ጀምሮ ኤደንን እንዲጠብቁና ምድርን በልጆች እንዲሞሉ በመፍቀድ እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ በእርሱ ፈንታ እንድንሰራ መፍቀዱን አስታወቀ።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ!” (1ኛ ዮሐንስ 3:1)።

ሀብትን በመስጠትም ባርኮናል፣ ነገር ግን ገንዘብ መሰብሰብን፣ ቼክ መጻፍን፣ ገንዘብን በኤሌክትሮኒክ መንገዶች ማስተላለፍን፣ ባጀት ማዘጋጀትን ወይም በሰንበት ቀን አሥራትንና ሥጦታን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማምጣትን የመሳሰሉ ሥራዎችን እንድንሰራ ለእኛ ሀላፊነት ሰጥቷል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሀብት ለራሳችን እንድንጠቀም፣ ሌሎችን እንድንረዳበትና የእርሱን ሥራ እንድንሰራበት ያበረታተናል። የማይታመን ቢመስልም እግዚአብሔር ልጆቹን የማሳደግን፣ ሕንፃዎቹን የመገንባትንና ቀጣዩን ትውልድ የማስተማርን ሀላፊነት የሰጠው ለእኛ ነው። በዚህ ሳምንት ትምህርት የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል የመሆንን መልካም ዕድሎችና ሀላፊነቶች እንመረምራለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለታህሳስ 29 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

እሁድ ታህሳስ 23 Jan 01


እኛ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ነን


“ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ ከሚሰየምበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አባት ፊት እንበረከካለሁ” (ኤፌሶን 3:14፣ 15፤)። በዚህ ጥቅስ ላይ ወደ ትውስታ የመጣው ምስል ምንድር ነው? በዚህ ውስጥ ምን ተስፋ ይገኛል?




ኢየሱስ በአገልግሎቱ ጅምር ላይ እንዲህ ብሏል፡- “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ስምህ ይቀደስ” (ማቴዎስ 6:9፣)። ከዚያ በኋላ በግል ለደቀ መዛሙርቱ ያንኑ ጸሎት ይደግምላቸዋል (ሉቃስ 11፡ 2)። ኢየሱስ አባቱን ‹‹በሰማይ ያለህ አባታችን›› ብለን እንድንጠራው ነግሮናል። ማርያም ኢየሱስን ከትንሣኤው በኋላ ባገኘች ጊዜ ልታቅፈው ፈለገች። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላት፣ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት” (ዮሐንስ 20:17)። ከኢየሱስ ጋር ተመሳሳይ አባት ስላለን፣ እርሱ ወንድማችን ስለሆነ፣ እኛ ሁላችንም በጌታ የእርሱ ወንድሞችና እህቶች ነን። እኛ የሰማያዊው ቤተሰብ አባላት መሆን እንድንችል ኢየሱስ የምድራዊው ቤተሰብ አባል ሆነ። “የሰማይ ቤተሰብና የምድር ቤተሰብ አንድ ናቸው”—ኤለን ጂ ኋይት፣ የዘመናት ምኞት ገጽ 832። ዘጸአት 3፡10፣ ዘጸአት 5፡1፣ እና ገላትያ 3፡26፣ 29ን አንብቡ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስላለው ግንኙነት እነዚህ ጥቅሶች ምን ይላሉ? ይህ ሊያደፋፍረን የሚገባው ለምንድር ነው?




ፍጥረት ቀዝቃዛና ጥንቃቄ የሌላቸው የተፈጥሮ ህጎች ውጤት እንደሆነ ከሚገልጸው አመለካከት በተቃራኒ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር መኖሩን ብቻ ሳይሆን እንደሚወደንና በቃሉ ውስጥ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ለመግለጽ የቤተሰብ ምሳሌ ጥቅም ላይ በዋለበት ሁኔታ ከእኛ ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደሚፈልግ ያስተምሩናል። ኢየሱስ እሥራኤልን ‹‹ሕዝቤ›› ብሎ መጥራቱ ወይም እኛን ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› ብሎ መጥራቱ ወይም እግዚአብሔርን ‹‹አባቴ›› ብሎ መጥራቱ ተመሳሳይ ነው፡-እግዚአብሔር እኛን የሚወደን የቤተሰብ አባሎች እርስ በርሳቸው መዋደድ ባለባቸው ሁኔታ ነው። ይህ እጅግ በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ እንዴት ያለ መልካም ዜና ነው! ሁሉም ሰው እንደ ቤተሰብ የሚታይበትን ዓለም አስቡ። ከሰብአዊ ፍጡራን ሁሉ ጋር ወንድማዊና እህታዊ ግንኙነት መፍጠርን እንዴት መማር እንችላለን?

ሰኞ ታህሳስ 24 Jan 02


እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ባለቤት ነው


መዝሙር 50:10–12፤ መዝሙር 24:1፤ 1ኛ ዜና 29:13፣ 14፤ እና ሐጌ 2:8ን አንብቡ. እዚህ ላይ ያለው መልእክት ምንድር ነው? ይህ እውነት ለእኛ እና እኛ ካለን ነገር ጋር ስላለን ግንኙነት ምን ይላል?




በ1ኛ ዜና ከምዕራፍ 17 ጀምሮ ያለው ክፍል ንጉሡ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት ለመስራት መፈለጉን ይዘግባል። ይህን ፍላጎቱን ‹‹እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ›› ላለው ለነቢዩ ናታን አካፈለ። (1ኛ ዜና 17:2)። ነገር ግን በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ለናታን መጣለትና ንጉሡ ጦረኛ ስለነበረ የእግዚአብሔርን ቤት መስራት እንደማይችል እንዲነግረው መመሪያ ሰጠው። ሥራውን ልጁ እንደሚሰራውም ተገለጸ። ዳዊት ቢያንስ ዕቅዶቹንና ለግንባታ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማዘጋጀት ይችል እንደሆነ ጠየቀ። ዳዊት ለጥያቄው አዎንታዊ መልስ ካገኘ በኋላ ቀሪ ሕይወቱን በሙሉ ያሳለፈው ለግንባታ የሚያስፈልግ ጥርብ ድንጋይ፣ የግራር እንጨት፣ ብረት፣ ወርቅ፣ ብርና ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የማይችል ነሃስ ሲያከማች ነበር። ለግንባታ የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ በግንባታ ቦታው ከተዘጋጁና ከተከማቹ በኋላ ዳዊት የእሥራኤልን መሪዎች በሙሉ ለውዳሴና ለምስጋና ሥነ-ሥርዓት ጠራቸው። ንጉሡ ዳዊት በ1ኛ ዜና 29፡13፣14 ላይ በሕዝብ ፊት በጸለየው ጻሎት ውስጥ እርሱና ሕዝቡ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማዘጋጀት ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ስላፈሰሱበት ለግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እውነተኛ ምንጫቸው ምን ነበር ያለው? እንዲህ ነበር ያለው፡- “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ስለሆነ፣ ለአንተም የሰጠነው ከአንተ የተቀበልነውን ብቻ ስለሆነ እኛ ምንም ዓይነት ምሥጋና ልንቀበል አንችልም።” ድሃም ብንሆን ሀብታም (በተለይም ለሀብታሞች) ነጥቡ ለሁላችንም አስፈላጊ ነው ። እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሁሉንም ነገር ስለፈጠረ (ዘፍጥረት 1፡ 1፤ ዮሐንስ 1፡3፤ መዝሙር 33፡6፣ 9ን ይመልከቱ)፣ የፈለገውን ያህል ለፍተን፣ ጥረንና ግረን በታማኝነት ያፈራነው ቢሆንም ያለንን ሀብት ጨምሮ በዓለም ያለው ነገር ሁሉ እውነተኛ ባለቤት በርግጠኝነት እርሱ ነው። ከእግዚአብሔርና ከጸጋው የተነሣ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር አይኖረንም ነበር፣ እኛም ምንም ሆነን እንቀር ነበር፤ እንዲያውም አንኖርም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር የሁሉም ነገር ባለቤት እንደሆነ ሁልጊዜ በመገንዘብ፣ ለእኛ ስላደረገልን በጎነት እያወደስነውና እያመሰገንነው በመኖር፣ ይህን ወሳኝ እውነት በፊታችን ማቆየት እንችላለን። “ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?” (1ኛ ዜና 29:14)። በእነዚህ ቃላት ውስጥ የተገለጹት መርሆዎች እንዴት ያማሩ ናቸው! ቃላቶቹ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ንብረታችን ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን መሆን እንዳለበት እንዴት ነው የሚገልጹት?

ማክሰኞ ታህሳስ 25 Jan 03


ለእግዚአብሔር ቤተሰብ የተዘጋጁ ሀብቶች


እግዚአብሔር ለልጆቹ ከሚሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ ትልቁ ስጦታ ይቅር የመባል ሰላም፣ ለዕለታዊ ሕይወትና ለመንፈሳዊ እድገት ጸጋን እና የዘላለም ሕይወት ተስፋን የሚያመጣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐንስ 3:16)። “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐንስ 1:12)። ስለዚህ ድነት መሰረታዊ ስጦታ ስለሆነ ያለዚህ ስጦታ ከእግዚአብሔር ምን ዋጋ ያለው ነገር ማግኘት እንችላለን? እዚህ ሊኖረን የሚችል ማንኛውም ነገር ቢኖር አንድ ቀን ስለምንሞትና ስለምንሰናበት፣ የሚያስታውሰን ማንኛውም ሰውም ሆነ ያደረግነው መልካም ነገር ሁሉ ይረሳል። ስለዚህ ከሁሉም አስቀድመን የወንጌልን ስጦታ፣ ያውም የተሰቀለውን ክርስቶስን፣ ሁልጊዜ የሀሳቦቻችን ሁሉ ማዕከል አድርገን መጠበቅ አለብን (1ቆሮ. 2፡2)። ሆኖም፣ ከድነት ጎን ለጎን፣ እግዚአብሔር ሌሎች ብዙ ነገሮችን ይሰጠናል። ለምግባቸውና ለልብሳቸው ለሚጨነቁ ሰዎች ኢየሱስ እንዲህ በማለት ማጽናኛ ሰጥቶአቸዋል፡- “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ. 6:33)። መዝሙር 23፡1፣ መዝሙር 37፡ 25 እና ፊልጵስዩስ 4፡19ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር የእለት እንጀራችንን የሚሰጠን ስለመሆኑ ምን ይላሉ?




ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለመሄዱ በተናገረ ጊዜ አጽናኙን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል ገባላቸው። “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ” (ዮሐንስ 14:15–17)። “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል…” (ዮሐንስ 16:13)። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ራሱ ለእግዚአብሔር ልጆች አስደናቂ የሆኑ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይሰጣል (1ኛ ቆሮ. 12:4–11ን ይመልከቱ)። በአጭሩ፣ “በእርሱ ሕያዋን ሆነን የምንንቀሳቀስበትና የምንኖርበት” እግዚአብሔር (የሐዋ. ሥራ 17:28)፣ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ የሚሰጥ” እግዚአብሔር (የሐዋርያት ሥራ 17:25)፣ ለሌሎች በረከት እንድንሆን ሕልውናን (መኖርን)፣ የድነት ተስፋንና መንፈሳዊ ስጦታዎችንም ሰጥቶናል። በድጋሚ፣ ምንም ዓይነት ቁሳዊ ሀብት ቢኖረንም፣ በምንም ዓይነት ሥጦታዎችና መክሊቶች ብንባረክም፣ በእነዚያ ሥጦታዎች አጠቃቀማችን በሁሉም መንገድ ለሰጪው ባለዕዳዎች ነን።

ረቡዕ ታህሳስ 26 Jan 04


የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ሀላፊነቶች


ሁላችንም እግዚአብሔር የሚሰጠንን መንፈሳዊና ሥጋዊ በረከቶችና ስጦታዎች እንደሰትባቸዋለን። እኛ ‹‹የቤተሰቡ አካል›› መሆናችንን ማወቃችን ደግሞ እንዴት ያጽናናል። ዘዳግም 6፡5ን እና ማቴዎስ 22፡37ን ያንብቡ። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ልንተገብረው እንችላለን?




እግዚአብሔርን “በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም” እንዴት መውደድ ትችላለህ?(ማቴ. 22:37)። በሚያስደንቅ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ መልስ የሚሰጥ ሲሆን መልሱም ብዙ ሰዎች እንደሚጠብቁትም አይደለም። ዘዳግም 10፡12፣ 13ን እና ዮሐንስ 5፡3ን ያንብቡ። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አባባል ከሰማያዊ አባታችን ጋር ስለሚኖረን የፍቅር ግንኙነት የእኛ ተገቢ መልስ ምንድር ነው?




ሕግን መጠበቅ ነው? ትዕዛዛቱን መታዘዝ ነው? እንደ አለመታደል ሆኖ ለብዙ ክርስቲያኖች ሕግን መታዘዝ (በተለይም አራተኛውን ትዕዛዝ)፣ ሕጋዊነት ስለሆነ በቀላሉ እግዚአብሔርን እንድንወድና ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ እንደተጠራን ይናገራሉ። ነገር ግን በዚህ ነጥብ ላይ እግዚአብሔር ግልጽ ነው፡ለእግዚአብሔርና ለባልንጀራችን ያለንን ፍቅር የምንገልጸው ትዕዛዛቱን በመታዘዝ ነው። “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” (1ኛ ዮሐንስ 5:3)።ይህንን ጥቅስ በተመለከተ እግዚአብሔርን ስለምንወድ ትዕዛዛቱንም እንደምንጠብቅ አድርገን ማየትን ልማድ አድርገናል። መልካም ነው። ነገር ግን ትዕዛዛቱን በመጠበቅ የእግዚአብሔርን ፍቅር ስለምናውቅና ስለምንለማመድ ‹‹የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነው›› ብለን ማንበብም እንችላለን። በማቴዎስ 7:21–27 ላይ ቃሉን ሰምተው የሚያደርጉ ሰዎች ቤቱን በዓለት ላይ የሰራ ጠቢብ ሰው ይመስላሉ በማለት ኢየሱስ ተናግሮአል። ሰምተው የማያደርጉ ሰዎች ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ በሰራ ሰነፍ ሰው ተመስለዋል--ውጤቱም አስከፊ ነው። ሁለቱም ቃሉን ሰምተዋል፣ አንዱ ሲታዘዝ ሌላኛው እምቢተኛነትን መርጦአል። ውጤቱ በሕይወትና በሞት መካከል ልዩነት ፈጥሮአል። እግዚአብሔርን በመውደድና ትዕዛዛቱን በመጠበቅ መካከል ስላለው ግንኙነት ያስቡ። ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር በዚህ መንገድ የሚገለጸው ለምንድር ነው? በርግጥ ትዕዛዛትን መጠበቅን በተመለከተ ያንን ፍቅር የሚገልጽ ነገር ምንድር ነው? (ፍንጭ፡- ሕጉን አለመታዘዝ ምን እንደሚያስከትል ያስታውሱ)።

ሀሙስ ታህሳስ 27 Jan 05


ሀብት (መዝገብ) በሰማይ


“ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” (ማቴ. 6:19–21)። ኢየሱስ በዚህ ቦታ እየተናገረ ያለው ስለምን ወሳኝ እውነቶች ነው?




በሆነ መንገድ ማጣታቸው የማይቀረውን ታላቅ ሀብት ያጋበሱ ሰዎችን ታሪክ በተከታታይ ያላነበበ ማነው? ዓለማችን በፍጹም ያልተረጋጋ ቦታ ነው፡- ጦርነት፣ ወንጀል፣ አመጽ፣ የተፈጥሮ መቅሰፍቶች ወይም ማንኛውም ነገር ሊመጣና በቅጽበት ዕድሜያችንን በሙሉ ለፍተን ያፈራነውን ሀብት ሊወስድ ይችላል፤ ያውም በታማኝነትና በቅንነት ያፈራነውን ሀብት። ደግሞ ሞት በቅጽበት ይመጣና ያሉን ነገሮች ሁሉ የማይጠቅሙን ሆነው ይቀራሉ። በርግጥ ሀብታም መሆን ወይም ሀብት ማፍረት ስህተት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በፍጹም አይነግረንም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሁሉንም ነገር በአግባቡ እንድንይዝ ያስጠነቅቀናል። ሀብት በሰማይ ማከማቸት ማለት ምን ማለት ነው? ገንዘብን ከሁሉም ነገር ከማስቀደም ይልቅ እግዚአብሔርንና የእርሱን ሥራ ከሁሉ በፊት ማስቀደም ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ያለንን ነገር ለእግዚአብሔር ሥራ፣ የእርሱን መንግስት ለማስፋፋት፣ ለሌሎች ለመስራትና ለእነርሱ በረከት ለመሆን መጠቀም ማለት ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር አብርሃምን በጠራው ጊዜ በእርሱና በቤተሰቡ አማካይነት የምድር ቤተሰቦችን በሙሉ ለመባረክ ሊጠቀምበት አቀደ። በያዕቆብ 2፡ 23 ላይ “የእግዚአብሔርም ወዳጅ” ተብሎ ስለተጠራው አብርሐም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- “ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” (ዘፍጥረት 12:2፣ 3)። “እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ” (ገላትያ 3:9)። ለእርሱ እንደቀረበ ሁሉ ለእኛም ተመሳሳይ ግድድሮሽ ቀርቦልናል። “ገንዘብ ትልቅ ሥራ መስራት ስለሚችል ትልቅ ዋጋ አለው። በእግዚአብሔር ልጆች እጅ ያለ ገንዘብ ለተራቡት ምግብ፣ ለተጠሙት መጠጥ፣ ለተራቆቱት ልብስ፣ ለተጨቆኑት መብት ማስከበሪያና ለታመሙት እርዳታ ነው። የሌሎችን ችግር ለመፍታት፣ ሌሎችን ለመባረክና የክርስቶስን ሥራ ለማስፋፋት ጥቅም ላይ ካልዋለ ገንዘብ ከአሸዋ የተሻለ ዋጋ የለውም። ”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 351. “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” (ማቴ. 6:21)። መዝገብህ ስላለበት ቦታ ልብህ ምን ይነግርሃል?

አርብ ታህሳስ 28 Jan 06


ተጨማሪ ትምህርት


“የእግዚአብሔር ልብ ለምድራዊ ልጆቹ ከሞት በጠነከረ ፍቅር ይናፍቃል። ልጁን አሳልፎ በመስጠት ሰማይን በሙሉ በአንድ ስጦታ አፈሰሰልን። የአዳኙ ሕይወት፣ ሞትና ምልጃ፣ የመላእክት አገልግሎት፣ የመንፈስ ቅዱስ ተማጽኖ፣ አብ ከሁሉም በላይና በሁሉም ውስጥ መስራት፣ የማያቋርጥ የሰማያዊ ፍጡራን ፍላጎት--ሁሉም ለሰው ልጅ መዳን ሥራ ላይ ውለዋል።”—Ellen G. White, Steps to Christ, p. 21. “ራስህን ከካድክና አንተነትህን ለክርስቶስ አሳልፈህ ከሰጠህ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ስለሆንህ በአብ ቤት ያለው ነገር ሁሉ የአንተ ነው። አሁን ባለው ዓለምና ሊመጣ ባለው ዓለም ያሉ የእግዚአብሔር ሀብቶች በሙሉ ለአንተ ተከፍተውልሃል። የመላእክት አገልግሎት፣ የመንፈሱ ስጦታ፣ የአገልጋዮቹ አገልግሎቶች ሁሉ ለአንተ ናቸው። እስከጠቀመህ ድረስ ዓለምና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ያንተ ነው።”—Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, p. 110.

40 views0 comments
bottom of page