• Admin

"ለዘንድሮ ብቻ ተዋት"

በአገራችን 2010 አመተ ምህረት ከገባ 3 ወር አለፈው። በምዕራብ አገሮች ደግሞ በቅርቡ 2018 ይገባል። ሁሉም በየበኩሉ አዲሱን አመት ለመቀበል ሽርጉድ ይላል። በአገራችን "እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገራችሁ" እንባባላለን። በምእራብ አገሮች ደግሞ "happy new year" ይባባላሉ።


ትኩር ብለን ካሰብንበት ያልጠፋነው፣ እዚህ የደረስነው፣ በህይወት ያለነው፣ በሰላም የምንወጣው የምንገባው፣ የምንንቀሳቀሰው ከእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት የተነሳ ነው (ሰቆቃው ኤርሚያስ 3፣22)። የእግዚአብሔር ጥበቃው ስለበዛልን፣ ምህረቱና ቸርነቱ ስለበዛልን፣ ሌሎች ያላገንኙትን ዕድል እነሆ እኛ ልናገኝ ነው — አዲስ አመት፣ አዲስ ዘመን፣ አዲስ አመተ ምህረት ብለን ልንጀምር ነው።


ጌታ የሱስ ሉቃስ 13፣6-9 ላይ ስለ አንዲት የበለስ ዛፍ እንደ ምሳሌ አድርጎ የተናገረው ታሪክ አለ። ይህች የበለስ ዛፍ ከሌሎች ዛፎች ለየት የሚያደርጋት ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው የተተከለችው በወይን እርሻ ቦታ ውስጥ ነው። እንደሌሎች ዛፎች መንገድ ዳር አልነበረችም ወፍዘራሽም አልነበረችም። ታቅዳ ታስባ የተተከለች ነበረች። ሁለተኛው የሚንከባከባት ሰራተኛ ነበራት፣ በዕድልሽ እደጊ የምትባል ሳይሆን ሞግዚት የተቀጠረላት ነበረች። ሁለቱም ነጥቦች የሚነግሩን እንክብካቤና ጥንቃቄ ይደርግላት እንደነበረ ነው።


እንግዲህ እንደዚህ አይነት እንክብካቤና ጥንቃቄ የተደረገላት ዛፍ ምን ይጠበቅባታል? ፍሬ!! ባለቤቱም ፍሬ ፍለጋ፣ የሚገባውን ፍላጋ፣ መብቱን ፍላጋ ተመላለሰ፣ እንዲያውም 3 አመት ተመላለሰ። ፍሬ ግን አላገኘባትም። ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ስላመዘነበት፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስላመዘነበት፣ የዛፊቱ የመኖሯ ትርጉሙ ፍሬ ስለነበረ፣ ፍሬም ስላላፈራች ባለቤትየው ለሰራተኛው "ቁረጣት" አለው። ትቆረጥ! ትጥፋ! ምን ታደርጋለች? እንዲያውም ሌላውን ትጎዳብኛለች፣ "ቁረጣት" አለው።


የተቀጠረላትም ሰራተኛ ብዙ ስለለፋባት፣ ስለተንከባከባት፣ ከበለሷ ዛፍ ጋር ፍቅርም ስለያዘው ትዕዛዙን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም፣ ሆዱ እሺ አላለውም፣ እጁም አልታዘዝ አለው ስለዚህም ጌታውን እንዲህ ብሎ ለመነው ጌታ ሆይ "ዘንድሮን ብቻ" ስጥኝ "አንድ አመት ብቻ" ጨምርልኝ "አንድ ዕድል ብቻ" ስጥኝ፤ ለዘንድሮ ብቻ ተዋት። ለከርሞ ታፈራለች!! አለው።


ወገኔ! የበለሲቱ ዛፍ እኛ ነን። እንደ በለሲቷ ዛፍ እንክብካቤና ጥንቃቄ የተደረገልን፤ የእግዚአብሔር ምህረት የበዛልን ነን። እኛም ፍሬ እንድናፈራ ይጠበቅብናል። አንድ አመት የተጨመረልን ፍሬ እንድናፈራ ነው እንጂ እንዲሁ ቦታ እንድናጣብብ ወይም "አፈሩን በከንቱ እንድናሟጥጥ" አይደለም።


እነሆ ጩኸታችንንና ልመናችንን ሰምቶ ጌታ አንድ አመት ሊጨምርልን ነው። ከርሞ ፍሬ ፍለጋ ሲመጣ ምን አይነት ፍሬ ያገኝ ይሆን? ወደዛፋችን ጠጋ ሲል ምን ያገኝብን ይሆን? ፍሬ ወይስ ዝም ብሎ ቅጠል? መልካም የፍሬ አመት!!


ዳንኤል ኃይለማርያም (ስዊድን) ዋና አዘጋጅ

34 views0 comments

Recent Posts

See All

እንደምን አደጋችሁ?

በፓስተር መላክ አለማየሁ ካለፈው የቀጠለ ባለፉት ሁለት ክፍሎች በመንፈሳዊ ሕይወታችን ስለ ማደግ ጠቅለል ባለ መልኩ መግቢያ የሚሆንን ሃሳብ ለማየት ሞክረናል። የፈጠረንና የዋጀን እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አላማ እለት እለት ወደ በረከቱ ሙላት እንድናድግ መሆኑ ቃሉ አስተምሮናል። እንዲሁም፣ በጸጋ ማደግ የሚከቱትን ሦስት

እንደምን አደጋችሁ?

ካለፈው የቀጠለ “እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም። የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል። እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና

“መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ…”

በአለፉት ሶስት ወራት ጌታ በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤተክርስትያን ከመስከረም 2010 ጀምሮ እስከ ህዳር መጨረሻ ድረስ ያደረገዉን ድንቅ ስራ ሳበሰር ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኢትዮጵያ ዉስጥ ወንጌል የአልገባባቸዉ እጅግ ብዙ ስፈራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መሀል አንዱ የዳሰነች ጎሳ ሲሆን፣ ጌታ ፈቅዶ በመጋቢት ወር አዲስ

የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋሺንግተን ዲሲ

© 2018 Ethiopian Seventh-day Adventist Church Washington DC

1700 Powder Mill Rd, Hillandale, MD 20903, U.S.A  301-356-5259

  • Facebook Social Icon
  • YouTube Social  Icon
  • Google Places Social Icon
  • Twitter Social Icon