• Admin

እንደምን አደጋችሁ?


በፓስተር መላክ አለማየሁ

ካለፈው የቀጠለ

ባለፉት ሁለት ክፍሎች በመንፈሳዊ ሕይወታችን ስለ ማደግ ጠቅለል ባለ መልኩ መግቢያ የሚሆንን ሃሳብ ለማየት ሞክረናል። የፈጠረንና የዋጀን እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አላማ እለት እለት ወደ በረከቱ ሙላት እንድናድግ መሆኑ ቃሉ አስተምሮናል። እንዲሁም፣ በጸጋ ማደግ የሚከቱትን ሦስት አቅጣጫዎች እንደሚያቅፍ ተመልክተናል:-


• በማምለክ ማደግ-ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የፍቅር ህብረት ይመለከታል

• ደጋፊ በመሆን ማደግ-በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ካሉ ወንድም እህቶቻችን ጋር ያለንን ህብረት ይመለከታል

• ግዴታችንን በመወጣት ማደግ-ከእግዚአብሔር ርቀው ያሉትን ፍቅሩን በማንጸባረቅ ወደ እርሱ ማደምን ይመለከታል


እነዚህ ሦስቱ የእድገት አቅጣጫዎች ማደግ በሚለው ምጻረ ቃል ሊታውሱ ይችላሉ።

በዚህ የጥናታችን ክፍል ደግሞ ወደ ክርስቶስ መስቀል ትኩረታችንን እናደርጋለን። ጌታችን በመስቀል ደሙን በማፈሰስ የከፈለው ድንቅ መስዋእትነት፣ ከላይ በተጠቀሱት ሦስት አቅጣጫዎች ለማደግ እንድንችል እንዴት ሃይል እንደሚሆንን እናጠናለን።


የመስቀሉ ሃይል በማምለክ ለማደግ


አምልኮ ማለት ለእግዚአብሔር ፍቅር የምንሰጠው ምላሽ እንደመሆኑ፣ የመለኮትን ፍቅር በጥልቀት መረዳት በማምለክ ለማደግ አማራጭ የሌለው ጎዳና ነው። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር ደግሞ ተወዳዳሪ ባልተገኘለት ድምቀት የተገለጠው በመስቀል ላይ አምላካችን ራሱን ለእኛ አሳልፎ በሰጠበት ጊዜ ነበር። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ:- “ነገር ግን ገና ሃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” ሮሜ 5:8


በመስቀል ላይ የተገለጠው ይህ ፍቅር ወደ እርሱ የሚያቀርበንና ከእርሱም ጋር የጠበቀ ህብረት እንዲኖረን አቅም የሚሆነን ነው። በመስቀል ላይ ከጌታችን አጠገብ ተስቀለው ከነበሩት ሁለት ውንበዴዎች መካከል አንደኛው ይህንን ፍቅር ለአፍታ ባስተዋለ ጊዜ በንስሃ ልቡ ተሞልቶ ከአምላኩ ጋር የነበረውን ግንኙነት አደሰ። (ሉቃ 23:40-43)።

እኛም የመስቀሉ ፍቅር ሲገባን ከክፉ መንገዳን ተመልሰን፣ ለሃጢአት ጀርባችንን ሰጥተን፣ የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም በሙሉ ልባችን እንገዛለታለን። ከሚጠፋውና ከሚያጠፋው የዚህ አለም ሃሳብ ይልቅ የእርሱን መንግስት እንመኛለን።


የመስቀሉ ሃይል ደጋፊ በመሆን ለማደግ


በክርስቶስ መስቀል የተገለጠው ፍቅር የጥልን ግድግዳ በማፍረስ እርስ በርሳችን በፍቅር እንድንተሳሰርና እንድንደጋግፍ የሚያስችለንንም ሃይል ይሰጠናል።

“ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤… ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። ኤፌ. 2: 14, 16


ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ በብዙ ጣእርና ስቃይ ከተናገራቸው ሰባት ቃላት መካከል ሁለቱ ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳዩ እንደሆኑ እናያለን። ሊያድናቸው የመጣው የገዛ ወገኖቹ በጠላትነት በመስቀል ላይ ሰቅለው በፊቱ ሆነው ሲዘባበቱበት ስለ እነርሱ እንዲህ አለ:- “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሉቃ 23:34። በእርሱ ላይ በደረሰው ልቡዋ በሃዘን ተስብሮ ከመስቀሉ ግርጌ ለነበረቸው እናቱ ለማርያም “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤ ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። (ዮሐ 19: 26፣ 27) ይህ ንግግሩ ከራሱ ስቃይ ባሻገር ለሌሎች በፍቅር በማስብ ያደረገውን የፍቅር ድርጊት የሚያሳይ ነው።

በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ስንኖር፣ ወዳጆች እንዲሁም ጠላቶች ይገጥሙናል። በመስቀል ላይ የተገለጠው ፍቅር ታዲያ ጠላቶቻችንን ይቅር እንድንል፣ ወዳጆቻችንንም እንድንከባከብ ግድ ይለናል። የቀራኒዮ ፍቅር የገባት ነፍስ ቂም አትይዝም። በራስ ወዳድነት አትዋጥም። ይልቁንም ያንኑ ፍቅር ለሌሎች ታካፍላለች።


የመስቀሉ ሃይል ግዴታችንን በመወጣት ለማደግ


የመስቀሉ ፍቅር የገባው ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፣ ወንጌልን የምሰብከው ግዴታዬ ሰልሆነ ነው” ብሎ ይጽፋል። ታዲያ ወንጌልን ለሌሎች በማካፈፍል እንዲህ እንዲተጋ ግድ የሚለው ምን እንደሆነ ሲጽፍ ደግሞ እንዲህ ይላል:- “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል” 2 ቆሮ 5:14፣ 15። በእርግጥም በመስቀሉ የተገለጠው የመለኮት ፍቅር ሃይል የራቁትን የሚያቅርብ፣ የቀርቡትንም ሩቅ ያሉትን ይፈልጉ ዘንድ የሚያነሳሳ ሃይል አለው። በመስቀሉ ግርጌ የነበረው የጌታ ደቀ መዝሙር ዮሐንስ፣ ከመስቀሉ በፊት የሰማርያ ሰዎች የጌታን አገልግሎት ለመቀበል ባልፈለጉበት ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲበላቸው የተመኝቶ ነበር (ሉቃ 9:54)። በመስቀል ላይ ያየው ፍቅር ሲለውጠው ግን እንዲህ ብሎ ጻፈ:- “እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።” (1 ዮሐ 2:2) ለአለም ሁሉ የፈሰሰው ደም ወደ አለም ሁሉ እንድሄድና ይህንን ድንቅ የምስራች እንድናበስር ግድ ይለናል።

በመንፈሳዊ ህይወታችን በጸጋው ለማደግ ወደ ክርስቶስ መስቀል መመልከት፣ በዚያም ላይ የተገለጠውን የእርሱን ፍቅር የዘወትር ሃሳባችን ማድረግ አማራጭ የሌለው ጎዳና ነው። በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት እድገታችን የተስተጓጎለብን ብኖር፣ ዛሬ ወደ መስቀሉ እንመለከት ዘንድ መንፍሰ ቅዱስ ይጠራናል። ከዚያም መለኮታዊ የሆነው የፍቅር ሃይል በአምልኮ ህይወታችን፣ ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ህብረትና በተሰጠን ተልእኮ ይሄውም ወደ አለም ሁሉ ሄደን በጨለማ ለተዋጡ ሁሉ ብርሃኑን የማሳይትን ሃላፊነታችንን በመወጣት ረገድ እንድናድግ ያግዘናል። ጌታ እለት እለት ያሳድገን!

6 views0 comments

Recent Posts

See All

እንደምን አደጋችሁ?

ካለፈው የቀጠለ “እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም። የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል። እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና

“መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ…”

በአለፉት ሶስት ወራት ጌታ በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤተክርስትያን ከመስከረም 2010 ጀምሮ እስከ ህዳር መጨረሻ ድረስ ያደረገዉን ድንቅ ስራ ሳበሰር ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኢትዮጵያ ዉስጥ ወንጌል የአልገባባቸዉ እጅግ ብዙ ስፈራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መሀል አንዱ የዳሰነች ጎሳ ሲሆን፣ ጌታ ፈቅዶ በመጋቢት ወር አዲስ

"ለዘንድሮ ብቻ ተዋት"

በአገራችን 2010 አመተ ምህረት ከገባ 3 ወር አለፈው። በምዕራብ አገሮች ደግሞ በቅርቡ 2018 ይገባል። ሁሉም በየበኩሉ አዲሱን አመት ለመቀበል ሽርጉድ ይላል። በአገራችን "እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገራችሁ" እንባባላለን። በምእራብ አገሮች ደግሞ "happy new year" ይባባላሉ። ትኩር ብለን ካሰብንበት ያ

የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋሺንግተን ዲሲ

© 2018 Ethiopian Seventh-day Adventist Church Washington DC

1700 Powder Mill Rd, Hillandale, MD 20903, U.S.A  301-356-5259

  • Facebook Social Icon
  • YouTube Social  Icon
  • Google Places Social Icon
  • Twitter Social Icon